Sunday, August 25, 2013

ጋዜጦች ባሳለፍነው ሳምንት 

 ኢትዮ-ምኅዳር ማክሰኞ ነሐሴ 15/2005ዓ.ም.

 ·         ርዕሰ አንቀፅ፡ የሕግ የበላይነት እና የፍትህ ልዕልና ይከበር

“አንድ የመንግስት ሹመኛ እና አንድ የመንግስት ተቋም በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ እንደፈለገው አድርጎ ወንጀል ይጋግራል፡፡ ለይምሰል ከፊል   ሕጋዊ አካሄድ ይከተላል፡፡ እናም ንጹሃንን ያሳቅቃል፣ ያሳስራል፣ ያሰቃያል፣ ይጎዳል፡፡ ሃብት ይነጥቃል፡፡
በአንዲት ቀጭን ስልክ የመንግስት አስፈፃሚ አካ ጥሪ፣ ዜጋን  ከእለት ተዕለት ባተሌ ኑሮ ወደ አሥረኝነት ትቀየራለች፡፡ በዚህ ጊዜ ለምን ብሎ መጠየቅ ሞኝነት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ችግሩ የህግ አሊያም የህገመንግስት ሳይሆን፣ የተፃፈውን እና የሆነውን በአግባቡ ከመተግበሩ ቁርጠኝነት ማጣት ላይ ነው፡፡”

  •    ኢህአዴግን ጨምሮ አንድነት፣ ሠማያዊ፣ መድረክ እና ኤዴፓ ባለፈው ቅዳሜ በኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ በፀረ ሽብር አዋጁ ላይ ለሶስት ሰዓት የቆየ ውይይት ማካሄዳቸውን፤ መድረክን ወክለው የኦፌኮ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ በቀለ ነጋ፣ አንድነትን ወክለው አቶ ሃታሙ አያሌው፣ ሠማያዊን ወክለው የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ይልቃል ጌትነት እንዲሁም ኢህአዴግን በመወከል በሚኒስቴር ማዕረግ የጠቅላይ ሚ/ሩ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ እና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል መቅረባቸውን፤ መኢአድ ላይ እንዲሳተፍ አለመጋበዙን


  •  ባለፈው ሳምንት እሁድ ነሐሴ 12/2005ዓ.ም ሠማያዊ ፓርቲ በጽ/ቤቱ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን በመጋበዝ ‹ኢህአዴግ በፖለቲካ ፍልስፍና አይን ሲዳሰስ› በሚል ርዕስ ህዝባዊ ውይይት መካሄዱን፤ ዶ/ር ዳኛቸው ‹‹ኢህአዴግ እስካሁን ሕዝባዊ ቅቡልነትን አላገኘም›› በማለትም ሃሳባቸውን የለያዩ ፈላስፋዎችን ስራዎች እያጣቀሱ ከሀገራችን ነባራዊ የፖለቲካ ሁነት ጋር በማያያዝ ለቅቡልነት የሚከተለውን ትርጉም ማስቀመጣቸውን  “ ቅቡልነት ማት በፖለቲካ ውስጥ ምን ማለት ነው የሰው ልጅ አስተዳደር የሚያውቀው አስተዳደር ሁለት አይነት ነው፤ አንዱ በሕግ ሌላው ደግሞ በጉልበት ነው፤ ከዚህ አይዘልም፡፡ የሕዝብ ቅቡልነት ማለት ከጉልበት ወደ ህጋዊ አስተዳደር መሸጋገር ማለት ነው፡፡”

 
የኛ ፕሬስ ማክሰኞ ነሐሴ 15/2005ዓ.ም.

·         ርዕሰ አንቀፅ፡ ሕዝብ ኢህአዴግ የፈጠረውን ‹‹አምላክ›› የማምለክ ግዴታ የለበትም

“የኢህአዴግ ስብከትም ወደ ፍፁም ቅዱሰ ቅዱሳን የተቃረበው የአቶ መለስ የዘወትር ውዳሴና ሙጋሴ ከመልካም ተግባራቸው ጎን የጎደለውን ሰባራ ጎናቸውን መጠገን ላይ ቢያውለው የተሻለ ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ በአስተሳሰብ ውስጥ የፈጠረውን አምላክ ህዝብ እንዲያመልክለት የከፈተውን ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ገደብ ሊያበጅለት የሚገባ ይመስለናል፡፡”

  • የሃገር ሃብት ለግል ጥቅም በማዋል በሙሰኝነት ወንጀል የተጠረጠሩ ባለስልጣናትን እና ግለሰቦችን ዝርዝር የያዘው የፀረ ሙስና ሰነድ፤ ሕውሃት እና ብአዴን የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ መያዛቸውን እንደሚያሳይ፤ ተጠርጥረው ከታሰሩት፣ ንብረታቸው ከታገደባቸውና በዓይነ ቁራኛ ከሚጠበቁት ተጠርጣሪዎች መካከል 40 በመቶ ሕውሃት፣ 25 በመቶ የብአዴን፣ 15 በመቶ የኦህዴድ፣ 10 በመቶ የደህዴን፤ አባላቶች ሲሆኑ የቀሩት 10 በመቶ የሚሆኑት ባለሃብቶች፣ ደላሎችና ከፓርቲዎች ጋር ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው እንደሆኑ


ሪፖርተር እሮብ ነሐሴ 16/2005ዓ.ም.
·         ርዕሰ አንቀፅ፡ ሕዝብ ‹‹መልካም አስተዳደር በተግባር!›› እያለ ነው

“መንግሥት መልካም አስተዳደር መኖር አለበት ይላል ወይ? አዎን! ኢሕአዴግም በጉባዔው ብሏል፣ በውሳኔም አሳልፏል፡፡ በየቀኑ መግለጫ ይሰጥበታል፡፡ መልካም አስተዳደር እውን የማታደርጉ ወዮላችሁ ብሏል፡፡ የመልካም አስተዳደር አለመኖር አደጋንም ገልጿል፡፡
መንግሥትም ብሏል፣ ኢሕአዴግም ብሏል፣ ሕዝብም ሰምቷል፣ አዳምጧል፡፡  ጥያቄው የተባለው፣ የተወሰነውና ቃል የተገባው መልካም አስተዳደር የት አለ የሚል ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ‹‹መልካም አስተዳደር በተግባር!›› ነውና፡፡ በተግባር ያልታየ ነገር ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ›› ነውና፡፡ መንግሥት በፌዴራል ደረጃም በክልል ደረጃም ወደ ተጨባጭና አሳማኝ ተግባር ይግባ፡፡ ይናገር ሳይሆን ያሳይ፡፡ ”

  •   የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በፌዴራል ደረጃ በተለያዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ከተሰማሩ 55 የውጭና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች መካከል፣ 31ዱ፤ በእጃቸው ላይ ያለውን ሥራ ከ50 በመቶ በላይ ማጠናቀቅ ባለመቻላቸው ምክንያት በአዳዲስ የመንገድ ግንባታ ጨረታዎች ላይ እንዳይሳተፉ መወሰኑን

  •   የ2005 በጀት ዓመት ሥራ አፈጻጸምን መሠረት በማድረግ በአጠቃላይ በሠራተኞችና በባለሥልጣናቱ መካከል ስለነበረው ግንኙነት፣ በሥራ ወቅት በውስጥና በውጭ የነበሩ አጠቃላይ ሁኔታዎችን በሚመለከት እርስ በርስ ለመገማገም፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ሠራተኞች ከነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት አዳማ (ናዝሬት) መግባታቸውን፤ በቅርቡ የፍትሕ ሚኒስትር በሆኑት አቶ ጌታቸው አምባዬ መሪነት አዳማ የከተሙት ሠራተኞች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ዓቃቢያነ ሕግና የድጋፍ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ ከ800 እንደሚበልጡ መጠቆሙን


  • የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ መቋረጥ ለኢንዱስትሪዎችና ለዜጎች ፈተና መሆኑን

  
ሠንደቅ እሮብ ነሐሴ 16/2005ዓ.ም.

·         ርዕሰ አንቀፅ፡ ሕገወጥ ስደትን ለመታደግ ሕጋዊውን ማጠናከር ይገባል


“ማህበራዊ ችግሮች ባልተፈቱበት ሁኔታ ሕገወጥ ስደትን ጠዋት ማታ በመገናኛ ብዙሃን ስለተነገረ ብቻ የሚቆም ባለመሆኑ መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡ ምናልባትም ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ብቻ ሳይሆን ወደ አውሮፓና አሜሪካ ጭምር ሄደው ሰርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚረዱበት ሁኔታንም ማሰቡ ሕገወጥ ስደትን ለመቀነስ ቁልፍ ሚና ስለሚኖረው በዚህም ረገድ የተያዘው የመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫ ሊመረመር ይገባል፡፡”
 

  •  የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር የነበሩት አቶ እውነቱ ብላታ ደበላ ከያዙት ኃላፊነት ተነስተው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስቴር ዴኤታ ሆነው መሾማቸውን፤ አቶ እውነቱ የተሾሙበት ቦታ አቶ በከር ሻሌ በአሁኑ ወቅት የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ይዘው የነበሩት ቦታ ሲሆን አቶ በከር ከዚህ ኃላፊነታቸው ተነስተው የአዳማ ከንቲባ ሆነው ከተሾሙ በኋላም ከዘጠኝ ወራት በላይ ቦታው ክፍት ሆኖ መቆየቱ


  •  የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንዳንድ ሰራተኞች የኢህአዴግ የ2006 ዓ.ም እቅድ መስሪያ ቤቱ ካለበት መደበኛ ስራ ውጪ የገዢውን ፓርቲ ድርጅታዊ ስራ በልዩ ሁኔታ እንዲያስፈፅም ማስገደዱን መቃወማቸውን፤ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አብዛኛዎቹ ሰራተኞች መስሪያ ቤቱ በ2006ዓ.ም ድርጅታዊ ስራን ትኩረት ሰጥተው እንዲተገብሩ መደረጉ ሰራተኛው ለፍላጎቱ የመንግስትና የድርጅትን ስራ ቀይጦ እንዲሰራ የሚያስገድድ መሆኑን መናገራቸውን

  •  የአንድነት ለዴሞክራሲ ለፍትህና ፓርቲ (አንድነት) ለሦስት ወራት የጀመረውን የሕዝብ ንቅናቄ በመቀጠል በኦሮምያ ከተሞች ውስጥ ዘመቻውን እንደሚቀጥል ማስታወቁን፤ በኦሮምያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ እና በባሌ ዞን ባሌ ከተማ ትላንት እሁድ ነሐሴ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ስለሚኖራቸው ሰልፍ፤ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከተማም በተመሳሳይ እለት ሊደረግ የታሰበው ሰልፍበአስተዳደሩ ጥያቄ ለጳጉሜን 3 መተላለፉን

  • ሠማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የመብራት ኃይል እና በሚኒሊክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሾች ውስጥ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ቢያቅድም የአዳራሾቹ ባለቤቶች ፓርቲው ስብሰባ ለማካሄድ ከ አዲስ አበባ አስተዳደር የፈቃድ ደብዳቤ እንዲያመጣ መጠየቃቸውን፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ ለአዳራሽ የከፈላችሁበትን ደረሰኝ በማለቱ በቢሮክራሲያዊ በሆነ መንገድ አዳራሾቹን መከልከላቸውን

  •  በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ለተጠቁና በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኝተው ህክምናቸውን ለሚከታተሉ ከ36 በላይ ለሚደርሱ ህሙማን መርጃ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ የኪነ ጥበብ ምሽት ከነሐሴ 19 ቀን 2005ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ ሊካሄድ መታቀዱን በኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ ስራ አስኪጅ የሆኑት አቶ ማቲዎስ ወንዱ እና የፕሮግራሙ ሃሳብ አመንጪ የሆነቸው የሚስ አዲስ 125ኛ አሸናፊ የሆነችው ወ/ት ታምሩ ማሳወቃቸውን፤

  •  የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ‹‹መንግስት ለዜጎች መብት መከበር በቂ ጥበቃ ያድርግ›› በሚል ርዕስ 127ኛው የሆነውን ልዩ መግለጫ ማውጣቱን ፤ ሰመጉ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አርሲ ዞን የመንገድ ሥራ ላይ በተሰማራው የቻይና ድርጅት ማለትም CGCOC  (ሲጂሲኦሲ) ዲራ ማኛ መቻራ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ማህበር የሆነው የዳንዲ ደራርቱ አርሲ ሰራተኞች ማህበር አመራርና አባላት ላይ በአሰሪው የCGCOC ቻይናውያን አለቆች የደረሰውን እና እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት የተለያዩ ማስረጃዎችን መርምሮ እና ተከታትሎ መግለጫውን በዝርዝር አቅርቧል፡፡ (መግለጫው ለህትመት በሚመች መልኩ ታትሟል)


አዲስ አድማስ ቅዳሜ ነሐሴ 18/2005ዓ.ም.

·         ርዕሰ አንቀፅ፡ ከአህያ ጋር ብጣሪ በልታ ከፈረስ ጋር ገብስ ትበላለች

“እንደ ቡድሐ አመለካከት፤ ከአንድ አስተሳሰብ ጋር እኝኝ ብለን ከተጣበቅንና፤ “አንዱና አንዱ ዕውነት” ይሄ ብቻ ነው ብለን ካከረርን፣ ዕውነተኛውን ዕውነት የማወቅ ዕደላችንን እንዘጋለን። ዕውነት እንደሰው ደጃፋችሁ ቆሞ ቢያንኳኳም እንኳ የአዕምሮአችሁን በር ለመክፈት ዝግጁ አትሆኑም፡፡ ስለዚህ ስለ አንድ ዕውነት የምትገነዘቡበትን መንገድ ሥራዬ ብላችሁ መርምሩት፡፡ ተጠንቀቁ፡፡ የነገር ሁሉ መጀመሪያው፤ ከሃሳብ እሥር ነፃነትን ማወጅ ነው፡፡”

  •   የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ነብዩ ባዘዘው እና ባልደረባቸው አቶ መሳይ ትኩ፤ ነሐሴ 19/2005 ሊያካሂድ ያሰበውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማስተባበርና አንዳንድ ዝግጅቶችን ለማድረግ ረቡዕ ፍቼ ከተማ ደርሰው እንደነበረ እና ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ባረፉበት ሆቴል በከተማው የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ሃላፊና ሌሎች ፊታቸውን በሸፈኑ 11 ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውና ራሳቸውን ሲስቱ ጥለዋቸው መሄዳቸውን፤ የዞኑ ኦህዴድ ጽ/ቤት  “ወደ ስፍራው ከመድረሳቸው በፊት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አላሳወቁም” የሚል ምላሽ እንደሰጠ

  •   ዘንድሮ ብቻ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በዳኝነት ሙያ ያገለግሉ የነበሩ መቶ ዳኞች ስራ መልቀቃቸውን፤ከ86 በላይ ዳኞችም የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው መልስ እየተጠባበቁ እንደሆነ፤ ዳኞቹ በደሞዝ ማነስ ፣በጥቅማጥቅም ማጣት፣በእርከን እድገት አለመኖርና በስራቸው ላይ በሚደርስባቸው ጣልቃ ገብነት ከስራ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ምንጮች መግለፃቸውን፤ ነገር ግን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ በበኩላቸው፤ መረጃው የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ እንዳስተባበሉ


 
ሪፖርተር እሁድ ነሐሴ 19/2005ዓ.ም.

·         ርዕሰ አንቀፅ፡ ኢትዮጵያን ያኮሩትንና ያከበሩትን እናክብራቸው! የላቀ ሥራ በመሥራት እንከተላቸው!

የአቶ መለስን ታሪክ ስናስታውስ መለስ ብለን ወደኋላ ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሌሎች ባለውለታዎችን እንለይ፣ እናስታውስ፣ እናወድስ፣ መታሰቢያ እናቁም፡፡ 

ያለፉትን ታሪክ የሠሩ፣ አገርን ያኮሩና ያራመዱ መሪዎችንና ዜጎችን ስናስታውስ፣ በእነሱ ሥራና ውጤት ተኩራርተን ብቻ መጓዝ የለብንም፡፡ እነሱ የሠሩዋቸውን አዎንታዊ ተግባሮች ጠብቀን፣ መፈጸም ያልቻሉትን እኛ ፈጽመንና የላቀ ውጤት አስመዝግበን መሆን አለበት፡፡

  •  የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ የሙስና ተግባራት ዕርምጃ እንዲወሰድ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ተነጋግሮ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ

  •  ኢትዮጵያ የባንክ ኢንዲስትሪ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙትና በአንጋፋነታቸው የሚታወቁት የግል ባንኮች በ2005 በጀት ዓመት በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተባለ የትርፍ ቅናሽ ማሳየታቸውን